የአፍሪካ የፊልምና ቴሌቪዥን ድራማዎች ሽልማት - በሌጎስ

ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ ያሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በተከናወነው የ2023ቱ አዋርድ ከተለያዩ አገራት የተወከሉ በርካታ ፊልሞችና ግለሰቦች ለውድድር ያመለከቱ ሲሆን በደቡብ አፍሪካዊቷ ሞዴል ዞዚቢኒ ቱንዚ እና በናይጄሪያው ስመ-ጥር የቴሌቪዥን አቅራቢአይክ ኦሳኪዮዱዋ አዝናኝ በሆነ አቀራረብ ለአራት ሰዓታት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ታግዞ በሌጎስ ኤኮ ሆቴልና ኮንቬንሽን ማዕከል ተከናውኗል፡፡

MVCA Awards night.jpg

Africa Magic Viewers Choice Awards (AMVCA) event in Lagos, Nigeria on May 20, 2023. Credit: D.Kebede

በግዙፉ አኅጉር አፍሪካ ግዘፍ የሚነሱ ባህልና እሴቶች አሉ፤ አንዳንዶች ዓለም አውቆ ያደነቃቸው ሲሆን ብዙዎች ከእይታና ተጋልጦ ተደብቀው እንኳን ዓለም ራሳቸው ባለታሪኮቹ አፍሪካውያን እዚህ ግባ አይሏቸውም፡፡

ከአውታረ ዜናዎች በላይ የፊልም ባህልና እሴት አስተዋዋቂነት አሌ የሚባል አይደለም፡፡ አሜሪካ በሆሊውድ የዓለምንና ቀልብ ስትስብ ህንድ ደግሞ በቦሊውም የዓለምን ልብ ማርካለች፡፡ ብራዚል በተፈጥሯዊ ዶክመንተሪ፣ ቻይናና ሩስያ ደግሞ ሚሊተሪ ሳይንስ ዶክመንተሪዎች ለዓለም ህዝብ ራሳቸውን እወቁልኝ እያሉ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የምዕራብ አፍሪካዋ ግዙፍ ባለኢኮኖሚ ናይጀሪያ “ኖሊውድ” የእኔ መተዋወቂያ ይሁነኝ ብላ እየሠራችበት ነው፡፡

ሰሞኑን ታዲያ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ሌጎስ ውሃ የተንተራሰና የነዋሪውን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ፊልም ሰሪዎችን ቀልብ የሰረቀ ታላቅ ሽልማት ተከናውኗል፡፡

ከግዙፉ የአፍሪካ የመዝናኛ ይዘቶች አቅራቢው መልቲቾይስ አፍሪካ አማካኝነት የሚቀርበው “የአፍሪካ ማጂክ ተመልካቾች ምርጫ ሽልማት - Africa Magic Viewers’ Choice Award /AMVCA/” በኖሊውድ ማህጸን ስር እልፍ የናይጀሪያ ዝነኞችን ጨምሮ ከደቡብ፣ ምዕራብና ምስራቅ አፍሪካ አገራት የተወከሉ ስመ-ጥር ተዋናዮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተከናውኗል፡፡

በአፍሪካ የፊቸር ፊልም፣ የቴሌቪዥን ድራማ እና ዶክመንተሪ ስራዎች የላቀ ጥራት ያላቸው ይዘቶችና የጎላ ስራ ከውነዋል ተብለው በተመልካቾችና በከፍተኛ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተመረጡ አርቲስቶች የሚሸለሙበት ታላቅ የአህጉሪቱ የሽልማት ስነ-ስርዓት ነው - አኤምቪሲኤ!

“አዋርዱ” እኤአ ከ2013 ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን ቀድሞ ናይጀሪያንና ኖሊውድን መሰረት አድርጎ ቢጀመርም ዛሬ አድማሱን አስፍቶ መልቲቾይስ የሚሰራባቸውን አፍሪካዊ አገራት ያካተተ “አህጉራዊ ሽልማት” ለመሆን በቅቷል፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቹ የአፍሪካ ኦስካር ሲሉ የሚጠሩት፡፡

የሽልማቱ ስነ-ስርዓት አፍሪካ ማጂክ በተሰኙ ቻነሎች በ50 አገራት ቀጥታ የሚሰራጭ መሆኑ ግዙፍነቱን ያሳያል፡፡ ኖሊውድ ውስጥ ሌጎስ መከናወኑ ደግሞ ደማቅና የዜና አውታሮችን ቀልብ ሳቢ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ከኮቪድ ወረርሺኝ በኋላ የተከናወነው የ2022ቱ 8ኛው አዋርድ የአማሪካ ሆሊውድ ፈርጦቹ Tasha Smith, Sidra Smith, Bayo Akinfemi and Grant Housley በክብር እንግድነት የተገኙበትና የሶሻል ሚዲያ ይዘት አቅራቢ ኪነ-ጠቢባን በሽልማት ዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱበት በመሆኑ በልዩ ድምቀት ተከውኖ አልፏል፡፡ 33 ያህል የሽልማት አይነቶችንም እውቅና ሰጥቶ ነበር፡፡

ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ ያሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በተከናወነው የ2023ቱ አዋርድ ከተለያዩ አገራት የተወከሉ በርካታ ፊልሞችና ግለሰቦች ለውድድር ያመለከቱ ሲሆን በደቡብ አፍሪካዊቷ ሞዴል Zozibini Tunzi እና በናይጄሪያው ስመ-ጥር የቴሌቪዥን አቅራቢ Ik Osakioduwa አዝናኝ በሆነ አቀራረብ ለአራት ሰዓታት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ታግዞ በሌጎስ ኤኮ ሆቴልና ኮንቬንሽን ማዕከል ተከናውኗል፡፡

በ35 ዘርፎች የተከናወነው AMVCA አህጉራዊ አዋርድ ዕድሜ ዘመናቸውን ለዘርፉ መጎልበት ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉትን ደማቅ ባለታሪኮችንና የአፍሪካ ተስፋ የሆኑ ወጣት ጠቢባንን በሽልማቱ አንበሽብሻል፡፡ በባህላዊ ትርኢቶችና ወርክሾፖች ታጅቦ ለ3 ተከታታይ ቀናት ተከናውኗል፡፡
2023 MVCA Winners.jpg
2023 MVCA Winners. Credit: D.Kebede

በሽልማቱ ናይጀሪያውያን የበለጠ ደምቀው የታዩ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ዑጋንዳ እና ታንዛኒያ ባለሙያዎችም ሽልማቱን ተቋድሰዋል፡፡ ናይጄሪያዊቷ የኖሊውድ ፊልም ንግስት Patience Ozokwor የህይወት ዘመን አስተዋጽኦ ተሸላሚ ሆናለች፡፡:

ሽልማቱ ከግለሰባዊ አበርክቶ በተጨማሪ በትወና፣ በይዘት፣ በምስል ቀረጻ፣ በድምጽና መሰል ቴክኒካዊ የጥራት መለኪያዎች እንዲሁም በአፍሪካዊ ቋንቋዎች የተሰሩ ይዘቶችን ለውድድር መስፈርት የተጠቀመ ሲሆን በየዓመቱ አዳዲስ ዘርፎችንም ያካትታል፡፡

ከ2024 እኤአ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች ለውድድር እንዲሳተፉ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መልቲቾይስ ያሳወቀ ሲሆን በአቦል ቴሌቪዥን የተላለፉትን ጨምሮ ሌሎች የፊልም ስራዎችና ግለሰብ ባለሙያዎችም ለዚህ አህጉራዊ ሽልማት መወዳደር እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከ35 አሸናፊዎች ዝርዝር ውስጥ ለመካተት አልበቁም።

ደመቀ ከበደ - ሌጎስ - ናይጄሪያ




Share
Published 22 May 2023 11:57pm
By Demeke Kebede
Source: SBS

Share this with family and friends