"ፍቅር ፍርንባዬ ድረስ ነበር የያዘኝ፤ ማሰብና መናገር እስኪያቅተኝ ድረስ" ድምፃዊ ኤልያስ "ኪዊ"

Kiwi SBS II.jpg

Singer Elias "Kiwi" Yemane. Credit: SBS Amharic

Get the SBS Audio app

Other ways to listen

"የማትፈታህ ሚስት ሙዚቃ ነች" የሚለውና በቀዳሚ ክፍለ ግለ ሕይወት ትረካው ከውልደት እስከ ምሽት ክለብ ጅማሮው ያወጋው ድምፃዊ ኤሊያስ "ኪዊ"፤ ትረካውን የምሽት ክለቡ ከቸረው የጥበብና የፍቅር ሕይወት እስከ ለጥቆ አገር ሲፈር እማኝ አስከ ሆነባትና ዝናን እስካተረፈባት የሶማሊያ ስደት አሻግሮ ያጋራል።


ድምፃዊ ኤሊያስ "ኪዊ" ቤተሰቦቹ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቀዬአቸው ለሽርሽር ድሬዳዋ ሳለ ከመወለዱ፣ አባቱ ሊቀጠበብትየማነብርሃን ዳምጤ ምንም እንኳ ልጃቸውን ዲያቆን ሆኖ ማየት ቢሹም፤ የዘመናዊ ሙዚቃ አፍቃሪና የድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ሁነኛ ወዳጅ የነበሩት አጎቱ የሙዚቃ ፍቅር ተፅዕኖዎች ከቀበሌ ለከፍተኛ መድረክ አድርሶ ዘፈኖቹ በምሽት ክለቦች የድምፃውያን ማይክሮፎኖች ውስጥ ናኝተው፤ ለታዳሚዎች ጆሮ ደርሰው፤ ዳንኪራ ማስረገጥ መቻላቻው ላይ ነበር ቀዳሚ ታሪኩን አርግቶ ይደር ያለው።

ቸራ የነፈገች ምሽት ክለብ

በድምፀ ቅላፄ ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የ200 ብር ተከፋይና የሚወደውን ሙዚቃ መድረክ ላይ ሆኖ ማጣጣም መቻል የአዲስ አማላይ ሕይወት ጅማሮ ነበር።

ፍቅር ላይ የወደቀው ግና ከሙዚቃ ሕይወቱ ጋር ብቻ አልነበረም። የአንዲት የባንዱን ጨዋታ ለመመልከት ብቅ ትል የነበረች ጉብልዬ ፍቅርም ታከለበት።

አሰኘው።

መታደል ሆኖ ግና ፍቅሩ ከኤልያስ በኩል ብቻ አልነበረም።

ጉብሊቱም አፍቅራው ነበር።

ከቶውንም ድምፁን ከማፍቀሯ የተነሳ "ስትናገር በዜማ አድርገው" ባይ ነበረች።

"ፍቅር ሲይዝህ የምታወጣው ድምፅና የምትፅፈው ግጥም ለየት ያለነው" እስከ ማለት የበቃ ዋቤነት ላይ አድርሶታል።

ሆኖም የጉብሊይቱ ቤተሰቦች ለሁለቱ የፍቅር ጉድኝት ቡራኪያቸውን በመንፈጋቸው ሳቢያ በአፍላው ተቀጨ።

ተለያዩ።

ፅኑዕ ፍቅር በትዝታ ሕይወትን ዘርቶ ይኖራልና፤ የጉብሊቱ ትዝታ ዛሬም ድረስ ውስጡ ሠርፆ አለ።

የውትድርና ሕይወትን ሁሉ ተቋቁሞ።

ዕጩ መኮንንነት

የኤልያስ ሕይወት 12ኛ ክፍል ሳለ የፍቅረኛውን መለየት ታክኮ ለዕጩ መኮንነት ኮርስ ወደ ሁርሶ ጦር ትምህርት ቤት አመራ።

የሙዚቃ ፍቅሩ ግና አልተዳፈነም።

ይልቁንም "The Kitchen Band" በሚል ስያሜ አንድ የሙዚቃ ቡድን አቋቋመ።

ዕውቅናንም አተረፈ።

በሕመም ምክንያት ስልጠናው ሳይጨርስ ቀረ።

በመኮንነት ማዕረግ ሳይመረቅ ከማሰልጠኛ ማዕከል ተሰናበተ።

ወደ ግራር ምሽት ክለብ ተመለሰ።

ስደት ከመውጣቱ በፊት።

ሶማሊያ

ኤልያስና ሶስትና ጉደኞቹ ሆነው መከሩ። ወሰኑ።

በጅግጅጋ አድርገው የአገረ ሶማሊያን ድንበር ተሻግረው ስደተኞች ሆኑ።

የስደት ሕይወት ፈተናዎችን እንደሚያበዛ ሁሉ ድንገተኛ ጥቂት ማለፊያ ዕድሎችንም ቸሪ ነው።

በሞቃዲሾ ስታዲየም የፖሊስ ኦርኬስትራን ለመመልከት ከጓደኞቹ ጋር የታደመው ኤልያስ በለስ ቀንቶት የዓሊ ቢራን "ቶሌ...ቶሌ" ለመዝፈን ያልታሰበ ዕድል አገኘ።

ዘፈነ፤ ሽልማት ጎረፈለት፤ ዝናም ተከተለ።

እምብዛም ሳይቆይ ግና የስማሊያ እርስ በእርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ።

ኤልያስ፤ አገር በጎሳ ጦርነት ታምሶ ሲፈርስ የታሪክ እማኝ ሆነ።

ያ ዕጣ ፈንታ ኢትዮጵያ ላይ እንዳይደርስ ዛሬም ድረስ በተማፅኖ ውስጥ ብርቱ ሕዝባዊ አመኔታን ውስጡ አሳድሮ አለ።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለውን ፅኑዕ አመኔታ አስባብ አድርጎም "አትፈርስም" ሲል አንድ ነጠላ ሲዲ እስከማውጣት ደርሷል።
Bemanim Atfersim .jpg
Credit: E.Yemane

ኤልያስ፤ የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት የስደት ፍቅረኛው ከሁለት ወር ፅንሷ ጋር ነጥቆታል።

ፍቅሩንና ታሳቢ ልጁን በሞት ያሳጣችውን ሶማሊያ ለቅቆም ኬንያ ለዳግም ስደት ተዳረገ።

ከኬንያ ስደት ካምፖች እንክርት በኋላ ለአገረ ኒውዝላንድ ሠፈራ በቃ።

ኒውዝላንድ ከተረጋጋ ሕይወት ትሩፋቶችዋም ባሻገር የሙዚቃ ሕይወቱን መልሳ ቸረችው።

ከማይክል ጃክሰን ጋር አገናኘቸው።

የኤልያስ ቀጣዩ የሕይወት ጉዞ የሚያመራው ከኒውዝላድ ወደ አውስትራሊያ ነው።
በተከታዩ ክፍል ይቋጨዋል።
 

 

Share